ዝርዝር

ሁሉም ስለ ልጆች

‘አበባ እና አበበ’ ወደ ቴሌቪዥን መስኮት የቀረቡላችሁ የተለያየ ክህሎት ባላቸው ሰዎች ጥምረት ሙሉ እውቀታቸውን የተጠቀሙበት ከተለያየ የዓለማችን ክፍሎች የተገኙ ኤክስፐርቶችና ፕሮፌሽናሎች(ጠበብቶችና ባለሞያዎች) እንዲሁም ከሃገራችን ኢትዮጵያ የተገኙ ባለሞያዎች በመሰባሰብ ችሎታቸውን በዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በተሰራ ስራ ላይ በማሳየት ነው፡፡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የመልቲሚዲያ ድርጅት የሆነው ታሜሶል ኮሙኒኬሽን እነኚህን በ52 ክፍል የቀረቡትን ተከታታይ የአኒሜሽን ፊልሞችን ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በየሳምንቱ ለእይታ አብቅቷል፡፡

የታወቁ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በማስተላለፍ የታቀው ታሜሶል ኮሙኒኬሽን ከዚህ ቀደም “ፎረም ሲኒማ” እና “የህገ-መንግስት የጥያቄና መልስ ውድድር” በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን በቅርቡም ለረጅም ጊዜ ሲያቀርብ የቆየውን ታዋቂውን የጠቅላላ እውቀት የጥያቄና መልስ ውድድር ማቅረብ ከጀመረ 9ኛ አመቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡እነዚሁ ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የተገኙ የአኒሜሽን ችሎታ ያላቸው ባለሞያዎች፣አርቲስቶች ፣ፕሮግራመሮች፣ኤዲተሮችና ዳይሬክተሮች “Toon Boom” የተባለውን የካናዳውያንን የአኒሜሽን መስሪያ ሶፍት ዌርን ስልጠና በበቂ ሁኔታ ወስደዋል፡፡ በኢትዮጵያ የስነ ዜጋ መፅሐፍት ዝግጅት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው የሚታመኑት ፀሐይ መላኩ፣ የዛና ወርቁ እና ወዳላት ገዳሙም ከዚሁ የአኒሜሽን ስራ ላይ በድርሰት ስራ ተሳትፈዋል፡፡

እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የአኒሜሽን ፅሑፎችን ፀሐፊ የሆነው በተለይም “ድራይቨር ዳን” እና “ፈን ዊዝ ክላውድ” (Driver Dan, Fun with Claude) በሚባሉት ፊልሞቹ የሚታወቀው ሳይመን ሮልፍ በነዚህ ተከታታይ ፊልሞች ላይ  ፅንሰ ሐሳቡን በማጎልበትና በማስተካከል ተሳትፏል፡፡ድምፆቹ የተሰሩት ልክ እንደኛ በሆኑ ህፃናት ሲሆን ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፣የስነ ዜጋ ትምህርት ይማራሉ፣ይጫወታሉ እና አሁን ደግሞ የዚህ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰራው ተከታታይ የልጆች አኒሜሽን ፊልም ላይ ተሳታፊዎች ሆነዋል!!